ምንኩስናና ገዳማት በኢትዮጵያ።
1/8/20251 min read


ክርስቲያናዊ የሆነ ገዳማዊ ኑሮ በኢትዮጵያ ማበብ የጀመረው የክርስትና ሃይማኖት የአገሪቱ ብሔራዊ እምነት ሆኖ በነገሥታቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው። የግብፃዊው የቅዱስ አንጦኒዮስን ገዳማዊ ሥርዓት የተከተለ በ 479 ዓ.ም. ወደ ሀገሪቱ የመጡት ዘጠኙ ቅዱሳን አስፋፍተውታል።
ስለዚህ ነው ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 7ኛው ክፍለ ዘመን ያለው ጊዜ ወርቃማው ተብሎ የሚታወቀው። በነዚህ ዘመናት ውስጥ ብዙ የስብከት ወንጌል ሥራዎች ተስፋፍተዋል፣ ልዩ ልዩ መንፈሣዊ ሥራዎችና ጽሑፎች የተከናወኑበት ጊዜ ነው። በአውሮፓ ያሉ ገዳማት የምዕራባውያንን ባሕል በመካከላለኛው ክፍለ ዘመን እንዲስፋፋና እንዲጠበቅ እንዳደረጉት ሁሉ በኢትዮጵያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትም የእውቀትና የሥልጣኔ ማዕከል በመሆን ሥነ ጽሑፎችን፣ ሥነ ሕንፃን፣ ቅኔዎችን፣ ዜማዎችን፣ ዝማሬዎችንና መንፈሣዊ ትምህርቶች እንዲዳብሩ አድርገዋል። በ5ኛው ክፍለ ዘመን የታወቀው የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ የቅድሴ ዜማዎችን፣ ዝማሬዎችንና ውዝዋዜዎችን በመፍጠር ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ይህ ለጆሮ ክፍተኛ ጣዕም ያለውን የምስጋናና የጸሎት ሥርዓት ያላትና የምትጠቀም በዓለም ያለች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን አድርጓታል።
