በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት አመጣጥ።

1/7/20251 min read

የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሐዋርያት ዘመን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑና ሌሎች ታሪካዊ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ። (ሐዋ. 826-36) ላይና በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳቢዮስ የኢትዮጵያው ጃንደረባ ጥምቀት በዓለም የመጀመሪያው የክርስትና እምነት ፍሬብሎታል በተጨማሪም ሩፊኖስ ቀጥሎም በቴዎድሬት፣ሶቅራጦስና ሶዝሜን ታሪክ ዘጋቢዎች ይህንን ታላቅ ሁኔታ ዘግበውታል። ይሁን እንጂ ክርስትና የመንግሥት እምነት ሆኖ በኤጲስ ቆጶስ ደረጃ መመራት የጀመረው በአራተኛው ክፍለ ዘመን በአክሱም ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይተረካል። ይኸውም የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስ አባ ፍሬሚናጦስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አድርጎ የሾመው በዘመነ አብርሃና አፅብሃ ጊዜ ነው። ንጉሥ ኤዛና በገንዘቦቹ ላይ የነበሩትን የጨረቃ ሥዕልን ቀይሮ የመስቀል ምልክት በማድረግ በዓለም ከነበሩት ነገሥታቶች መካከል ቀድምትነትን ቦታ አግኝቷል። በ356 .. አርያናው ንጉሥ ኮንስታንትዩስ ለአክሱም ንጉሥ ሲጽፍ ጳጳሱ ፍሬሚናጦስ የክርስትናን እምነት አጥፊ ስለሆነ ወደ ሮም ተይዞ ይላክብሎ ነበር። ነገር ግን ይህ ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝለት ቀርቷል። ቅዱስ ፍሬሚናጦስ በኋላ በኢትዮጵያውያን ኣባ ሰላማ (የሰላም አባት) ከሳቴ ብርሃን (የብርሃን ገላጭ) እየተባለ ሲታወቅ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የጳጳሳት መጠሪያ የሆነውን አቡን የሚባለው አጠራር ማለትም (አባታችን) ተቀብሎ ነበር።

የዘጠኙ ቅዱሳን (ተሰዓቱ ቅዱሳን) ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጎታል። እነዚህ ዘጠኙ ቅዱሳት በመባል የሚታወቁት ከወደ ቢዛንታይን ሥርወ መንግሥት በ479 .. ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ይነገራል። እነርሱም የሕዝቡን ቋንቋ ግዕዝን ተምረው ባሕሉን ተምረው መጽሐፍ ቅዱስንና ብዙ የተለያዩ መንፈሣዊ መጽሐፍትን ከዕብራይስጥ፣ ከግሪክና ከሲሪያክ ቋንቋዎች ወደ ግዕዝ ቋንቋ ተርጉመዋል፣ ወንጌል ከመስበካቸው በተጨማሪ ክርስቲያናዊ ገዳማትን በማቋቋም ገዳማዊ ሕይወት እንዲመሠረት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ የተሸጋገረችበት ወቅት ነበር። ይሄውም ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያንን ዜማ፣ቅኔና ዝማሬን አዘጋጅቶ ከአገልግሎት ላይ እንዲውል ያደረገበት ወቅት ስለነበረ። በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲይኗ ከፍተኛ እድገት

የታየባቸው ዘመኖች ከ4ኛ እስከ 7ኛው ክፍለ ዘመን ያሉት ወርቃማ የቤተ ክርስቲያን የእድገት ዘመኖች በመባል ይታወቃሉ።

ኢትዮጵያ በመካከለኛው አፍሪካ የክርስትና እምነት ማዕከል በመሆን የምትታወቅና የራሷ የሆነውን የክርስትና እምነቷንና ታሪኳን የጠበቀችና የነፃነት ምልክት በመሆን ለዘመናት ሁሉ የቆየች አገር ነች።